
24/07/2025
በሩሲያ ባጋጠመ የአውሮፕላን አደጋ የ48 ሰዎች ህይወት አለፈ።
ንብረትነቱ የአንጋራ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን ከራዳር እይታ ከጠፋ በኋላ ተከስክሶ ሲገኝ በውስጡ የነበሩ ሁሉም ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
42 መንገደኞች እና 6 የበረራ አባላትን አሳፍሮ የሀገር ውስጥ በረራ የጀመረው የሩሲያ አውሮፕላን ወደ ማረፊያው ሲቃረብ ከበረራ ባለሙያዎች ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡ እና ከራዳር መሰወሩ ተገልጿል።
በኋላ የሩሲያ ሲቪል አቪየሽን አውሮፕላኑ ተከስክሶ መገኘቱን እና ሁሉም ሰዎች መሞታቸው አስታውቋል። ከተጓዦቹ መካከል 5ቱ ህፃናት ናቸው።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰባት ክልላዊ ግዛት አስተዳዳሪ የ3 ቀናት የሃዘን አዋጅም አውጀዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አውሮፕላኑ በጫካ ውስጥ ተከስክሶ ሲያገኙት ከአካባቢው ምቹ አለመሆን ጋር ተያይዞ በቦታው ለመድረስ ሰዓታት ፈጅቶባቸዋል።
አውሮፕላኗ በአየር ማረፊያ ለማረፍ ያልተሳካ የመጀመሪያ ሙከራ ማድረጓ እና ዳግም ለማረፍ ስትሞክር የራዳር ግንኙነቱ መቋረጡ ተገልጿል።
አንቶኖቭ 24 የተሰኘችው አውሮፕላን ከ50 አመታት በላይ የቆየች ስትሆን በቅርቡ የተደረገላትን የቴክኒክ ፍተሻ ግን አልፋለች ተብሏል።
የሩሲያ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ከ2018 ወዲህ በእንደዚህ አይነት አውሮፕላን 4 ጊዜ አደጋ ማጋጠሙን ገልጿል።
በ2011 ይኸው የአውሮፕላን ስሪት አደጋ በደረሰበት ወቅት የወቅቱ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ አውሮፕላኖቹ ከአገልግሎት እንዲወጡ ጠይቀው ነበር።
Source: BBC