
09/19/2025
“አታውጡኝ… ሁለቱ ልጆቼ እጄን ይዘውኛል”💔
***
👤 በቴዲ ካሳ Teddy Kassa
እ.ኤ.አ. በታህሳስ 15 ቀን 1999 በቬንዙዌላ ውስጥ ቫርጋስ በተባለ አካባቢ ትልቅ የጭቃ ናዳ አደጋ ተከስቶ ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሏል፣ ከተሞችን በሙሉ ቀበሯል፡፡ በአደጋው ከ8ሺ በላይ ቤቶች ወድሟል፣ ከ10ሺ እስከ 30 ሺ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡም ይገመታል።
ይህ ልብ የሚሰብር ክስተት የፍቅርን እና የቤተሰብ ትስስርን ያሳየም ሆኖ አልፏል፤ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ይህ በምስሉ ላይ የሚታየው አባት በጭቃ ውስጥ ተይዞ ነበር። በስፍራው የደረሱ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ሊያወጡት ሲሞክሩ ልጆቹ እጁን እንደያዙት ስለተሰማው "አታውጡኝ፣ ልጆቼ እጄን ይዘውኛል" ብሎ መለሰላቸው። እጁን የያዙት ልጆቹን ትቶ እጁን ከእጃቸው መለያየት አልፈለገም። ይልቁንም እሱ ከልጆቹ ጋር እጅ ለእጅ እንደተያያዘ መሞትን መርጦ የራሱን ሕይወት መስዋዕት አድርጓል።
የዚህ የአባት የመጨረሻ ቃል የቫርጋስ አደጋ ምን ያህል አስከፊ እንደነበር ከማሳየቱም በላይ፣ ፍቅር ከሞት የበለጠ ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ አሳዛኝና ልብ የሚነካ ታሪክ ነው።
አንዳንድ መስዋእትነቶች ልዩ ናቸው። አንዳንዴ አንተ እየኖርክ ሌሎችም እንዲኖሩ የምትከፍለው መስዋእትነት አለ። በሌላ በኩል ደግሞ አንተ ሞተህ ሌሎች እንዲኖሩ የምትከፍለው መስዋእትነት አለ።
በዚህ ታሪክ ያየነው መስዋዕትነት ደግሞ አባትም ሆነ ልጆች ያልተጠቀሙበት፣ ማናቸውም ያልተረፉበት ነገር ግን እጃቸው ከእጁ እንዳይለያይ በመፈለግ፣ እጁ ከእጃቸው ተለያይቶ ቢተርፍ በህይወት ዘመኑ ሊሰማው የሚችለውን ፀፀት በመፍራት እንዲሁም አልጨክን ያለ አባትነቱን ያየንበት ልዩ መስዕዋትነት ነው።
ከዚህም ከዚያም
ጣዕም ሚዲያ