
09/15/2025
የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃቸው እና ረድኤታቸው አይለየን 🙏
ገና በ3 ዓመታቸው በገዳም መኖር የጀመሩና ከማሕጸን ጀምሮ ለመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የተለዩ፣ ከተወለዱ ጀምሮ እህል ያልቀመሱ፣ በምድረ በዳ እንደመላእክት የኖሩ፣ ስለሀገራችን መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው የጸለዩ፣ ከጌታችን ጋር መሞት አይገባኝም ብለው የተከራከሩ ታላቅ ጻድቅ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡፡
ትውልዳቸው ግብጽ ንሒሳ ውስጥ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ሠላሳ ሦስት ዓመት በትዳር ሲቆዩ በሩካቤ ስጋ የተዋወቁት ለሦስት ቀናት ብቻ ነው፡፡ ይህም ልጅ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን እየለመኑ ነው፡፡ በተጋቡ በሰላሳ ዘመናቸው አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን “ክብሩና ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢዩ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ” የሚል ድምጽ ሰማች፡፡
መጋቢት 29 ፀንሳ በታኅሣሥ 29 ደም ግባቱ እጅግ ያማረ ዓይናችን በገለጽንበት ቅጽበት ከሚታይ ነገር ላይ እንደሚያርፈው ሁሉ በተወለደበት ቅጽበት አንደበቱ ሲያመሰግን የተገኘ፣ ወንድ ልጅ ወለደች። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ “የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን” አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገዶ “ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን” አለ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ባረከችው ቅዱሳን መላዕክት ዘወትር ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሕፃኑን አባ ዘመደ ብርሃን የተባሉ አባት ላሉበት ገዳም ሰጣቸው፡፡
ሕፃኑንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ ትምህርቱን በጨረሰ ጊዜ ዲቁና ሰጡት፡፡
ፍጹም የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበታልና ሥራው ሁሉ በዕውቀት የተመላና የተቃና ሆነ፡፡ እንደ ቅዱስ እንጦንስም አስኬማ ሰጥተው አመንኮሱት፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቅስናን ተቀበሉና በጾም በጸሎት ተጠምደው በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ እንደ ሐዋርያትም የተአምራትና የፈውስ ሀብት ተሰጣቸውና ድውያንን የሚፈውሱ፣ ሙታንን የሚያነሡ፣ አጋንንትን የሚያወጡ ሆኑ፡፡ ወደ ሰማያት አርገው በረከትና ጸጋ የተቀበሉ፣ አጋንንትን የሚያሳድዱበት፣ ታላቅ ጸጋ ተሰጣቸው፡፡ ሰውነታቸው አንድ ክንድ ከስንዝር በሚረዝም ጠጉር የተሸፈነው አባታችን ወደ ሀገራችን መጥተው ተጋድሏቸውን ቀጠሉ፡፡
ከሰው ተለይተው ወደ ዱር ገብተው ከስድሳ አንበሶችና ከስድሳ ነብሮች ጋር የሚኖሩት አባታችን፣ እንስሳቱ እርሳቸውን የረገጡትን መሬት ልሰው ጠግበው ይኖራሉ። የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ገዳማቶቻቸው ወዳሉባቸው ወደ ምድረ ከብድና ወደ ዝቋላ ተራራ ወሰዳቸው፡፡ በእነዚህ ገዳማት እየተመላለሱ ሲጸልዩና ሀገራችንን ሲባርኩም ኖረዋል፡፡ ሰው የገዛ ፊቱን በመስታወት እንደሚያይ በሀገራች ያለውን የኃጢአት ስራ ባዩ ጊዜ በዝቋላ ሐይቅ አንድ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው መላው ኢትዮጵያን እንዲምርካቸው ጸልየው ቃል ኪዳን ተቀብለዋል፡፡ በመጨረሻም መጋቢት 5 በምድረ ከብድ አቦ ገዳም አርፈው ጌታችን በመላእክት ምስጋናና ዝማሬ ነድሳቸውን በታለቅ ክብር ተቀብሏታል። ገዳማውያን ይህን አብነት አድርገው ዓለምን ንቀው ለጌታችን ተገዝተዋል፤ ገዳማቱን እንርዳ በዓታችውን እናጽና፣ ከበረከታቸው እንካፈል፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444