06/19/2025
አገሩን አጋድሞ የሰየፋት ጀነራል
አንዳአንዴ አገራቸውን አጋድመው የሚያርዱ ዜጎች ይፈጠራሉ። የሆዳቸው እንጂ የአገራቸው ጉዳይ ፈጽሞ የማያሳስባቸው ሰው መሳዮች ይፈጠራሉ። በቃላት መግለጽ በማይቻል ደረጃ የአገራቸውን አንገት በዱልዱም ቢላዋ ካረዱት መካከል ኢራናዊው ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኤል ቃኒ ተጠቃሽ ነው።
የኢራን ፕሬዚዳንት መሐመድ አህመዲ ነጃድ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በአንድ የቱርክ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአረብኛ ፕሮግራም አንድ ጥያቄ ቀረበላቸው። ኢራን "የሞሳድን መረብ መበጣጠስ ያልቻለችበት ምክንያት ምንድነው?" የሚል። ተስፋ በቆረጠ ስሜት 'በፕሬዝዳንትነት ዘመኔ ለመበጣጠስ ቁርጠኝነቱ ነበረኝ፤ እናም በጣም ጥቂት ቁልፍ ታማኝ ሰዎች የተካተቱበት ኮሜቴ አዋቅሬ ነበር። ሆኖም ውጤቱ የምጠብቀው አልነበረም። አሁን መለስ ብዬ ስገመግም የኮሚቴው ሰብሳቢ ያደረግኩት ሰው የሞሳድ አባል ይመስለኛል' በማለት መለሱ።
ንግግራቸው አስቂኝ ቀልድ ተደርጎ ነበር የተወሰደው። ኢራንም ከቁብ አልቆጠረችውም። ምክንያቱም የኮሚቴ ሰብሳቢ አድርገውት የነበረው በኢራን እስልምና አብዮታዊ ጥበቃ ቡድን (IRGC) ስር የተደራጀው አል-ቁድስ (Quds Force) ልዩ ክፍል ምክትል አዛዥን ነበር። ኢራን በእሳት የተፈተኑ ወርቆች ከምትላቸው የጦር መሪዎቿ አንዱ ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኤል ቃኒ ነበር። አህመዲ ነጃድ ቃለ ምልልሱን በሚሰጡበት ወቅት ደግሞ ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኤል ቃኒ አሜሪካ ኢራቅ በድሮን ጥቃት የገደለቻቸውን ጀኔራል ሱሌማኒ ተክተው የአል ቁድስ ዋና አዛዥ ሆኖ ነበር (እኤአ ጥር 2020 አካባቢ ማለት ነው)። በዚህ ደረጃ የሚገኝን ቁልፍ የአገሪቱ ወታደራዊ አዛዥ መጠርጠር የማይታሰብ ነበር። ያውም በየመድረኩ አሜሪካ እና እስራኤልን የሚጠላና የሚያብጠለጥል፣ በሁለቱ አገራት ጥብቅ ማዕቀብ የተጣለበት፤ ሁል ጊዜ ለግድያ የሚዛትበት . . . ማንና እንዴት ይጠርጥረው? ኢራን አሁን በምርመራ እንዳረጋገጠችው ደግሞ ጀኔራል ሱሌማኒ በኢራቅ ባግዳድ የተገደሉት ቃኒ በሰጠው መረጃ ነበር።
ነገሮች በዛው ቀጠሉ፤ ኢራን አዳዲስ የመሬት ውስጥ ኑክሊየር ማብሊያዎችን ብትሰራም እንዳሰበችው መደበቅ አልቻለችም። ገና ሰርታ ሳትጨርስ መረጃው እስራኤል እጅ ይደርሳል። በስፍራው የሚሰሩ ሳይንቲስቶች ማንነት፣ አድራሽና እንቅስቃሴ ሁሉ ሞሳድ እጅ መግባቱን ቀጠለ። እስራኤል የፈለገችውን የኑክሊየር ሳይንቲስቲ በጠራራ ፀሃይ ያውም በአገሪቱ ዋና ከተማ መቅጠፍ ቀጠለች። የአሁኑ ይባስ እንዲሉ የአገሪቱ አምስት ቁንጮ ባለስልጣናት ብቻ የሚያውቁት የኢራን የኑክሊየር ሙሉ ሚስጥራዊ ሰነድ በእስራኤል እጅ ገባ። ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁም ጋዜጠኞችን ሰብስበው የኑክሊየር ሰነዱን በስክሪን እየገለጡ ማብራሪያና መግለጫ ሰጡ። ሆኖም ማንም ማንንም መጠርጠር የሚችልበት አንዳችም ክፍተት አልነበረም።
ይባስ ብሎም የሀማሱ መሪ እስማኤል ሀኒያ በሄሊኮፕተር አደጋ የሞቱት የኢራን ፕሬዝዳንት ቀብር ላይ ለመገኘት ወደቴህራን ባቀኑበት ወቅት ወደ ማረፊያ ክፍላቸው አስቀድሞ በገባ ቦንብ ተቀጠፉ። ከዚህ ሁሉ ጀርባ የኢራን ሁነኛ ባለስልጣን ጀነራል #ቃኒ ቢኖርም ማን ይጠርጥረው❓በምን ፍንጭ❓
በታሪክ ለእስራኤል ፈተና ከሆኑት የታጣቂ ቡድን መሪዎች መካከል የሂዝቦላ መሪው ሀሰን ናስራላህ ይጠቀሳል። የማይጨበጠው ናስረላህ ከሞሳድና ከዓለም ተሰውሮ የሚኖር የእስራኤል ራስ ምታት ነበር። ለዓመታት ለመግደል ያደረገችው ጥረት ሀሉ አልተሳካላትም። በጣት ከሚቆጠሩ የሂዝቦላ መሪዎች በስተቀር ማንም የማያገኘውና የማያውቀው፤ ብዙውን ጊዜውን በመሬት ውስጥ በተገነባ ቢሮና ማረፊያ ውስጥ የሚኖር ነበር። ይህ የመሬት ውስጥ የኮንክሪት ምሽግ እጅግ ስውር እና በጥንካሬው ወደር የሌለው ነበር። ይሁንና ባለፈው መስከረም ወር እስራኤል የሂዝቦላህን መሪዎች የሬዲዮ መገናኛዎችን በማፈንዳትና በተለያዩ መንገዶች ስትገድል ኢራን የናስረላህ ደህንነት አሳሰባት።
ለደህንነቱ ሲባል ለጊዜውም ቢሆን ወደ ቴህራን እንዲመጣ ፈለገች። ይሁንና በተደጋጋሚ ተጠይቆ ፍቃደኛ ባለመሆኑ አሳምኖ እንዲያመጣው ጀነራል ቃኒን ወደ ሊባኖስ ላከች። ሊባኖስ ሲደርስ ከዛ ቀደም መልእክት በሚለዋወጡበት መንገድ ለውይይት ቀጠረው። የቀጠሮው ቦታም ሌላም ጊዜ በሚሰበሰቡበት የናስረላህ የመሬት ውስጥ ቢሮ ነበር። ቀኑ ደግሞ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 28/2017 ነበር። ናስረላህ ጥቂት ምክትሎቹንና አጃቢዎቹን ይዞ የተለመደው ቦታ ደረሰ። ትንሽ ጠበቁት፤ ያልተለመደ ቢሆንባቸውም ፈጽሞ አልጠረጠሩትም፤ እናም መልእክት ላኩለት፤ "ችግር አጋጥሞኝ ነው፤ አልመጣም እናንተ ተሰብሰቡ" የሚል ምላሽ ሰጣቸው።
ወዲያውኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እና የእስራኤል ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሄርዚ ሃሌቪ በቤሩት ሲያንዥብቡ ለነበሩ የእስራኤል የጦር ጄት አብራሪዎች "ዝግጁ!" አሏቸው። በቅጽበት በአሜሪካ ሰራሽ “በንከር በስቲንግ” ቦምቦች በህንፃዎች ስር በጥንቃቄ የተሰራውን ናስረላህ የሚገኝበት የመሬት ውስጥ ዋሻ አፈራረሱት። ሁሉንም ገደሏቸው። አስመሳይዋ እስራኤል "ለዓመታት ተዘጋጅቼ" አለች። አብሮትም የኢራን አብዮታዊ ዘብ “ቁድስ ሃይል” መሪው 'ሳይገድለው አልቀርም' የሚል መረጃ አሰራጨች። ዓለም ዜናውን ተቀባበለው። ጀነራሉ ግን አይኑን በጨው ታጥቦ ወደአገሩ ኢራን ተመለሰ። ይሁንና ድምጹና ምስሉ ከሚዲያዎች ጠፍቶ ስለነበር ዓለም 'ተገድሏል' የሚል እምነት አሳድሮ ነበር። ይሁንና ኢራን ነገሮች አጠራጣሪ ስለሆኑበት እንደተመለሰ በቁጥጥር ስር አውላ ምርመራ ጀምራ ነበር። ከወራት በኋላ (የዛሬ 4 ወር አካባቢ) በቁጥጥር ስር አውላ እየመረመረችው መሆኗን ይፋ አደረገች።
ሆኖም ሁሉም ነገር 'ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ' ነበር። እስራኤል ላለፉት 20 ዓመታት በቃኒ በኩል በዘረጋችው የሞሳድ መስመር የአገሪቱን ቁልፍ መረጃዎች ቦጥቡጣ ወስዳ ነበር። ከዚህ በኋላ ጊዜ ማጥፋት አንድም ኢራን ኑክሊየር እንድትሰራ መፍቀድ ነው። ሁለትም ቀረኝ የምትለው አጠራጣሪ መረጃ የለም። እናም ለወራት ብቻ ዝግጅት አድርጋ ትናንት ሌሊት የጀመረችውን ፈጸመች። 200 የተለያዩ ጀቶችን አሰማርታ፣ የመሬት ውስጥ መንደርደሪያዎችን ሰርታ፣ ድሮኖችን አስገብታ . . . አስደንጋጭ ጥቃት ፈጸመች፤ አወደመች፤ የምትፈልጋቸውን የኢራን ቁልፍ ወታደራዊ አዛዦች ከነቤተሰቦቻቸው ፈጀች። እጅግ ውድ የኑክሊየር ሳይንቲስቶቿን ቀጠፈች። . . . ኢራን የአንድ ዜጋዋ ክህደት ያልጠበቀችው እና ያልገመተችው እየደረሰባት ይገኛል።
በእኛም አገር ተመሳሳይ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም። ብዙ ጀነራል ኢስማኤል ቃኒዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለአፍታም መዘናጋት ፈጽሞ አይገባም፤ ሲበdu እንኳን አይንን መንቀል አያስፈልግም።
Source Hanan federalist