01/25/2025
ዳ ያ ስ ፓ ራ ው 🇦🇺
* በደራሲ አዳሙ ተፈራ ተ/ሰማያት
| በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ኑሯቸውን በተለያዩ የአለም አገራት ከመሰረቱ ጊዜው
እራቀ። ቀደም ሲል እንደ ሀገር ክህደት ይቆጠር የነበረውም ስደት ተለመደ። መለመዱ ብቻ ሳይሆን ተናፋቂ አማራጭም ሆነ። ኢትዮጵያውያን በምድር ላይ ድምበር ሳያግዳቸው እግራቸው ያልረገጠው አገር አለ ለማለት ያዳግታል።
የዚህ ጽሁፍ አብይ አላማ ፣ ባለፉት 50 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው
የፓለቲካና ማህበራዊ ውጥንቅጥ ውጤት የሆነው ዳያስፓራ ታሪክ ለኢትዮጵያዊው አንባቢ በመጠኑም ቢሆን ለማድረስ ነው ። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፓራዎችን የሕይወት ተመክሮ ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች ለማስተዋወቅ። ስለኢትዮጵያዊው ዳያስፓራ አኗኗርና ስደት ሂደት ለማወቅ ለሚሻ አንባቢ፤ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ፣አጥኝዎች፣በተለያየ መንገድ ወደ ውጭ ለመውጣት ለሚያስቡ ኢትዮጵያውያን (ለትምህርት ለሥራ ወይም በስደት) መጠነኛ የመረጃ ምንጭ ሊሆን ይችላል። መጽሃፉ በ 11 አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፓራዎች አጫጭር ታሪኮች ላይ
ያተኮረ ነው። ብዛት፣ አሰፋፈርና ገጠመኝ ታሪኮችን ያወሳል። ስለሆነም ወድ አንባቢ በተለያየ አገር የሚኖሩ ወገኖቻችንን የሰፈራ ሂደት እየተዘዋወረ እንዲጎበኝ ይጋብዛል።የኢትዮጵያውያን ስደት ታሪክ ሁሉም በሚባል መንገድ የተጻፉት በእንግሊዝኛና በሌሎች የውጭ ቋንቋዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊው አንባቢ በአማርኛ እንዲያገኛቸው ታሳቢ ያደረገም ነው።
የአዘጋጁ ቀደምት ሥራዎችና አጭር ታሪክ
1. Say Goodbye to the Mountains: Refugee Stories from Ethiopia, by Nutsshell Graphics Pty ltd, Melbourne, 2003 (በተባባሪ አዘጋጅነት).
2. Struggles of Settlements in Horn of African Communities in Melbourne, Synergy, no 20, 2007 (ጥናታዊ ጽሁፍ መጣጥፍ).
3. የኢትዮጵያውያን ማንነት በባእዳን ቅኝት(መጽሃፍ) 2007 ቦሌ ማተሚያ ቤት
4. ገመናችን በሰው አገር፦ ኢትዮጵያውያን በአውስትራሊያ 2012 (ሁለተኛ እትም),
Minutmean Press-44 Buckley Street, Footscray VIC,
በአውስትራሊያ ከሚኖረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዳያስፓራ ማለትም ወደ 60 በመቶው ያህል በሚኖርበት የቪክቶሪያ ግዛት በአንዱና ትልቁ የአውስትራሊያ ሜልበርን ከተማ ከ20 አመታት በላይ በኢትዮጵያውያኑ ማህበረሰብ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከመሆኑም ሌላ በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር መሪነት ለብዙ አመታት አገልግሏል። በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያንን ማህበረሰብ አሰፋፈር አስመልክቶ በተለያየ ዘርፍ ማለትም በቤት ውስጥ አመጽ፣ወላጆች በአውስትራሊያ የትምህርት ሥርአት ውስጥ ልጆቻቸውን በማገዝ ረገድ ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚና ወዘተ የተለያዩ ጥናቶች ላይ ተሳትፏል።
በእነዚህና የተለያዩ ወቅታዊና ህብረተሰባዊ ፋይዳ ባላቸው ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ
በአውስትራሊያው SBS (Special Broadcasting Service) ራዲዮ አማርኛ ላይ የተለያየ ፕሮግራሞችን አቅርቧል።
አጫጭር ታሪኮች
▪ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ 1876 - 1922 ባሉት አመታት 35 ዜጎች ብቻ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ይኖሩ የነበሯት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በስደት በተለያዩ አገሮች ተበትነው ይገኛሉ። በ80ዎቹ ውስጥ ለዓለም ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ካበረከቱ ሶስት አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች።
▪ የኢትዮጵያውያኑ ስደት ወደ የመን የተጀመረው የመናውያኑ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በተደረገበት ወቅት የመናውያን ባሎቻቸውን ተከትለው በሄዱ ኢትዮጵያዊት ሚስቶች ነበር። የኢትዮጵያዊቶቹ ስደት በጥቅል ሲቃኝ በሁለት መንገድ ነበር ወደ የመን የተሰደዱት። በመጀመሪያ የመናውያን ባሎቻቸውን ተከትለው የሄዱት ሲሆኑ ሁለተኛው ለሥራና ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ በራሳቸው የተሰደዱት ናቸው። እርግጥ እነዚህ በዚህ መንገድ የተሰደዱ ሴቶች ገጠማኞቻቸውና የስደት
ልምምዳቸው ይለያያል።
▪ ካሊድ አቢይዱን የተባለ ሊባኖሳዊ የህግ ባለሙያ ወደ ሊባኖስ ለቤት ስራ የጎረፉትን ኢትዮጵያዊቶች አስመልክቶ በተለይ ከህግ አንጻር ችግሩን በፈተሸበት ሁለገብ ጽሁፉ ውስጥ በርካታ ብርቱ ጉዳዮችን አውስቷል።ካሊድ ስለኢትዮጵያዊቶቹ ለምን ለመጻፍ እንደተነሳሳ ምክኒያቶቹን ከዘረዘረልን በሃላ በመጨረሻው ላይ«እኔ አረብ የሊባኖስ ሰው ነኝ። እነዚህ ሴቶች በየእለቱ የሚጋፈጡትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ባይኔ አይቻለሁ። ያየሁት አሰቃቂ ስእል ከአእምሮዬ አልወጣ ስላለኝ ይህንን ጽሁፍ እንድከትብ አስገደደኝ» ብሏል። የካሊድ ጽሁፍ ርእስ «የሰለጠነው ዘመን አዳዲስ የባርነት መከሰቻ መንገዶች» የሚል ነው።
▪ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሰራተኞች መተዳደሪያ ህግ በመባል በሚታወቀው ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል። «የእጅሽንም ሆነ የእግር ጥፍሮችሽን ቀለም እንዳትቀቢ። ሱቅም ሲትሄጂም ቢሆን የመዋቢያ ቅባቶች እንዳትጠቀሚ። ጸጉርሽ አጭርና ንጹህ መሆን አለበት። በምትሰሪበት ሰአት የሚያጣብቅ ሱርኒ አጭር ካንቴራ እንዳትለብሺ። ወደ ሳሎን ቢጃማ ለብሰሽ እንዳትሄጂ።»
▪ የኢትዮጵያው ስደት ካናዳ ውስጥ የተጀመረው በ1980ዎቹ ውስጥ ነው። ያም የሆነው የካናዳው ዘረኝነት የተጠናወተው የስደት ፓሊሲ እየተቀየረና ዘር/ቀለም/ ተኮር መሆኑን እየተወ በመጣበት ወቅት መሆኑ ነው።
▪ ስደት ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደለም።አንድ የስደት አሉታዊ ገጠመኝ እነሆዎ። ወሩ ኦግስት ሲሆን 1995 ዓመተምህረት ነው። ስንዱ ታደሰ የተባለች የ 20 አመት ወጣት አብራት ትኖር የነበረችውን ትራንግ ፎንግ የተባለችውን የቬተናም ስደተኛ ተማሪ ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ካጠፋች በሃላ እራሷን ገደለች። ሁለቱም የሃርቨርድ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ ለሁለት አመት አብረው ኖረዋል። ስደትና ስደትን ተከትለው የሚከሰቱ እንደመገለል ብቸኝነት፤ ኑሮን መቋቋም ያለማቻልና የአእምሮ ጤና እውክታ የፈጠረው መጥፎ ፍጻሜ እንደነበረ በጉዳዩ ዙሪያ ያጠኑ
ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።
▪ የኒዘርላንድስ የስደተኛ አሰፋፈር ደረጃው ለየት ያለ ነው። ኢትዮጵያውያኑ ጥገኝነት ተፈቅዶላቸው ኒዘርላንድስ ከገቡ ቦሃላ የስደተኞች ጊዚያዊ መቀበያ ካምፕ እንዲቆዩ ይደረጋል። ወዲያው እግራቸው ኒዘርላንድስን እንደረገጠ የድጎማ/የዳረጎት/ ኑሮ ይጀምራሉ።ወደ መቀበያ ካምፕ እንደገቡ በመጀመሪያ ቃለመጠይቅ ይደረግላቸዋል። ከዚያም መሰረታዊ የቋንቋና የባህል ትውውቅ ስልጠና ይሰጣቸዋል።የመኖሪያ ፈቃዳቸው ጉዳይ ሳይወሰን ወደ ጊዚያዊ መቆያ ቤት
እንዲሄዱ ይደረጋል።በመጨረሻም ወደ ከተማ አስተዳደር ቤቶች እንዲዘዋወሩ ይደረጋል።ኪራዩን የሚከፍለው መንግስት ነው።የጥገኝነት መጠየቂያ ማመልከቻቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ መማርም ሆነ መስራት አይፈቀድላቸውም። ከኒዘርላንድ የስደተኞች ካውንስልና ከግል የህግ ባለሙያዎች የህግ ጉዳይ ነጻ ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ።
▪ ኦስትሪያ ውስጥ እንደሌላውም አገር ሁሉ ለኢትዮጵያውያኑ ትልቁ ማነቆና ዳገት የሆነው ጉዳይ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የማግኘቱ ነገር ነው።ኦስትሪያ ውስጥ ከገቡ በሗላ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ረዥም ግዜ ለመጠበቅ ይገደዳሉ። ይህም በመሆኑ ከነገዛሬ ካገር ያስወጡናል ወይም እንጠረዛለን በሚል በስጋት፣ በመጨነቅና መጠበብ ይኖራሉ። ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘቱ ጉዳይ ኑሮን ለመጀመር ቁልፍ ነው። ሥራ ለመቀጠር፣ ገቢ ለማግኘት፣ማህበራዊ ሕይወትን ለመገንባት፣ የጤና ዋስትና/ኢንሹራንስ ለማግኘት እና ከህብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል አስፈላጊ ነው።
▪ ጀርመን ውስጥ ከሚኖሩ ሌሎች አፍሪካውያን ጋር ሲነጻጸሩ ኢትዮጵያውያኑ በቁጥር የላቁ አይደሉም። በብዛታቸው መጠን ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር ሲነጻጸሩ በ 10 ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።ለምሳሌ በ 2007፤ 67,989 የሞሮኮ ዜጎች እንዲሁም 20,293 ጋናውያን ጀርመን ይኖሩ የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ 20,000 ይደርሱ ነበር። ዳሩ ግን ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያውያኑ ቁጥር ብልጫ አለው።ከ 1995 ጀምሮ እስከ 2007 የኢትዮጵያውያኑ ቁጥር ከ 15,305 ወደ 10,203 ዝቅ ብሏል።
▪ የኢትዮጵያውያኑን ከስዊዲን ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅሎ/ተዋህዶ/ መኖርን በተመለከተ የተካሄደ ጥናት ነበር። በጥናቱም መሰረት፤ የመዋሃዳቸው ሁኔታ የሚወሰነው በሁለት ጉዳዮች ላይ ነው። እነሱም በሰፋሪዎቹ በስዊዲን የቆይታ ጊዜና ጾታ እንደሆነ ተጽፏል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊቶች ሥራ ስምሪታቸው ከፍተኛ ሲሆን ከሕብረተሰቡ ጋር ከመዋሃድ አንጻርም የተሻለ ዝንባሌ ሊያሳዩ ችለዋል። በቅርብ አመታት ውስጥ የኢትዮጵያውያኑ ከስዊዲን ህብረተሰብ ጋር የመዋሃድ ሂደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተመዝግቧል።
▪ የአውስትራሊያ ከፍተኛው የማደጎ ምንጭ የኢሲያው አህጉር ሲሆን ከ 2009 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ 82 በመቶ የሚሆኑት የማደጎ ልጆች የመጡት ከዚያው ነው። ከዚሁ አህጉር ሶስቱ ዋና ዋና የማደጎ ምንጭ አገሮች፣ፊሊፒንስ 22 በመቶ ቻይና 14 በመቶና ደቡብ ኮሪያ 14 በመቶ ድርሻ ነበራቸው። ከኢስያ ውጭ ደግሞ አንዷ ዋነኛዋ አገር ኢትዮጵያ ስትሆን ድርሻዋም 15 በመቶ ነበር።
መጽሃፉ የሚገኝባቸው መደብሮች
o ጃፋር በ ሁሉም መጻህፍት መደብር
o ከድር - ለገሃር፣ አውቶብስ ተራ፣ አራት ኪሎና ቦሌ
ዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/
ፌስቡክ ገጽ: https://web.facebook.com/getu26
ቴሌግራም ገጽ: https://t.me/getutemesgenet
ቲክ ቶክ ገጽ: https://www.tiktok.com/
ኢንስታግራም ገጽ: https://www.instagram.com/getutemesgenet
ኤክስ: https://x.com/getutemesgenet
አማርኛ ድረ-ገጽ: https://amharic.getutemesgen.et
ኢንግሊዘኛ ድረ-ገጽ: https://getutemesgen.et