03/07/2025
መሸነፍ እና መታከት የትግላችን መዝገበ ቃላት ውስጥ የሉም። የአማራን ትላንት በቅጡ ያነበበ እና የተረዳ፤ የአማራን ዛሬ በሚገባ የተነተነ፤ የአማራን ነገ በጥንቃቄ የተለመ መሪ ይዘን የማንወጣው አረንቋ፤ የማንሻገረው ማዕበል የለም።
ይህ ትግል ብዙ አስከፊ ገጠመኞች፣ ብዙ ጀግኖች የሰሩት ተዓምር፣ ብዙ ገራሚ ክስተቶች ድር እና ማግ ሆነው ያቆሙት ቅዱስ ትግል ነው። ትግሉ በስርዓት እንዳይመራ እንቅፋት እየሆኑ ያሉት ከቅርብም ከሩቅም የእግዜር እንግዳ ብለው የተከሰቱ፣ የእናቶች ማቅ መልበስ የማያሳስባቸው፣ አንገታም ወንድሞቻችን በየአውደ ግምባሩ ጠላትን ተናንቀው ሲወድቁ ያላዩ፣ ለህዝብ እንዳልታገልን ሁሉ ለአንዱ ሜዳሊያ ሲታደል ለጥቂቶቻችን ደሞ ሞት ሲፈረድብን እንደነበረ የዘነጉ፣ በአጠቃላይ የትግሉን ምሬት እና ጣዕም የማያውቁ ናቸው።
ዛሬም እንደ አርዓያ የምናያቸው እንደ ወንድም የምናምናቸው ታጋዮች በየቀጠናው አሉ። አንድነቱ እንዳይፀነስ የነበረውን ግድግዳ ለማፍረስ ብዙ ዋጋ ከፍለን የምጥ ግዜው ላይ ደርሰናል። ግብግቡ የጨነገፈ ልጅ ይወለድ ወይስ ጤናማ ልጅ የሚለው ነው።
እጁን መሰብሰብ ያለበት እጁን ያነሳል፤ ከላኪወቹ የተሸከመውን ፕሮጀክት ሳይሆን የፋኖን ፕሮጀክት ሊያሳካ የሚፈልግ ካለ አብሮን ይታገላል። ይህ ትግል እንደ መንፈቅ ህፃን ልዩ ክትትል የሚፈልግ እንጅ የማንም ቅዠታዊ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ አይደለም።
አስረስ ማረ✍️